
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሁሉም ክልሎችና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልምድ ለመውሰድ ለመጡ አካላት ልምድ አካፈለ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሁሉም ክልሎችና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልምድ ለመውሰድ ለመጡ አካላት ልምድ አካፈለ።
ሰኔ 20ቀን 2017 ዓ.ም የአ.አ.ሴ.ሕ.ማ.ጉ.ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከሁሉም ኢትዮጵያ ክልል ለተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና ተወካዮች በቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም በከተማ ደረጃ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ዙሪያ ልምድ የማካፈል ፕሮግራሙን በልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች አከናውኗል።
በልምድ ልውውጡ የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ፣ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ልህቀት ማዕከል ም/ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር መሰረት ዘላለም፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመወከል የተገኙት ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በቢሮው የሕፃናት ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ተስፋዬ እንዲሁም በ ቢሮው የሕፃናት ዘርፍ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት እና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን ጨምሮ በርካታ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ተገኝተውበታል።
እለቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስጀመሩት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በክብርት ከንቲባ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረውና በአሁኑ ሰዓት በከተማችን በተለይም ቢሮው በሰጠው ልዩ ትኩረት እየተከናወነ የሚገኘው የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም የብዙ እናቶችን እና ሕፃናትን ተስፋ ያለመለመ እንዲሁም ከተማችንን ከሀገር አልፎ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለትውልድ ትኩረት የሰጠች ምቹ ተምሳሌት የሚያደርጋት መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ልህቀት ማዕከል ም/ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር መሰረት ዘላለም ስለፕሮግራሙ እና ስለ ማዕከላቸው ሲያብራሩ ከተማዋን አልፎ ሀገሪቱን ብሎም አፍሪካን ለሕፃናት እና ለእናቶቻቸው ምቹ በማድረግ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ በመሆኑ በየአመቱ ለቀደማይ ልጅነት እድገት ልማት ፕሮግራም የሚያዘውን በጀት በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት ከግማሽ ቢልየን ብር በላይ በጀት እንደተመደበለት ጠቁመዋል።
በእለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀዳማይልጅነት ልማት ፕሮግራም ማስተግበሪያ የአደረጃጀት ፣ቅንጅትና አሰራርን እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ቢሮው የሕፃናት ዘርፍ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት እና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በወ/ሮ ሕይወት ደረሰ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን የቀረበውን ሰነድ አስመልክቶም ውይይት ተካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያስተባበረው ይሄ የልምድ ልውውጥ በከተማ ደረጃ ቢሮው እየሰራ የሚገኙ ስራዎች አበረታች እና ስኬታማ በመሆናቸው እና ይሄንኑ የተሻለ ልምድ እና ውጤታማነት በተሻለ ለማስቀጠል እና ሀገር አቀፍ እንድምታ እና መስፋፋት እንዲኖረው በማለም የሁሉንም የሀገሪቱ ክልሎች እና ርዕሰ መስተዳደር ያካተተ ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመዋል።
በቢሮው የሕፃናት ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ተስፋዬ በበኩላቸው ፕሮግራሙ የክብርት ከንቲባችንን አርአያነትን በመያዝ በቁርጠኝነት የሚሰሩ የበርካታ ተቋማት እና ባለሙያዎች ውጤት በመሆኑ ይሄንን ለማሳደግ እና ሀገራዊ ፋይዳውንም ለመጨመር በትብብር እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
በእለቱ የጉብኝት ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን በጉብኝት መረሀ ግብሩም የተለያዩ አይነት የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት የሆኑትን በስራ ቦታ ላይ የሚቋቋሙ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት/ Work Place Day Care)፣ ማህረሰብ አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማዕከላት/community run ECD center/ ፣ሙሉ ወጪው በመንግስት የሚሸፈን የሕፃናት ማቆያ ማዕከል/public financed day care/ እንዲሁም እናቶች የቀን ማቆያ ማዕከል/day mother/ አገልግሎቶችን ተሳታፊዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎችም በእለቱ ለተደረገላቸው አቀባበል የሚኒስትር መ/ቤቱን እና ቢሮውን ያመሰገኑ ሲሆን በቆይታቸውም ስለ ቀዳማይ ልጅነት እድገት ልማት ፕሮግራም ምንነት እና አተገባበር በርካታ እውቀት እንደቀሰሙበት በመግለፅ በቀጣይም ፕሮግራሙን በየክልላቸው ተግባራዊ ለማድረግ ከክልል ርዕሰ መስተዳደር እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments