
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ተገለፀ።
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ተገለፀ።
ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም የአ.አ.ሴ.ሕ.ማ.ጉ.ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን አፈጻጸማቸውን የመከታተል፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ እና የአገሪቱ (የመዲናዋ) ዝርዝር የልማት እቅዶች የሴቶችን ፍላጎት ያገናዘቡ መሆናቸውን የማረጋገጥና የመሳሰሉት ቀዳሚ ግዴታዎች አሉበት፡፡
ቢሮው በተለይም በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል እና ከመግታት አንፃር የተለያዩ የአሰራር ዘዴዎች እና አደረጃጀቶችን በመጠቀም በርካታ ተግባራትን እና ንቅናቄዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
በዛሬውም ዕለት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ሲካሄድ የቆየውን ከተማ አቀፍ ንቅናቄ የማጠቃለያ መድረኩን በተለያዩ ሁነቶች አከናውኗል።
መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስጀመሩት የቢሮው ኃላፊ
ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ቢሮው በሀገሪቱ በተለይም በመዲናችን የሚከሰቱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ከማዕከል እስከ ወረዳ ባሉ ማዋቅሮቹ እና ከሁሉም ክ/ከተማ የተውጣጡ የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎችን በማስተባበር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አውስተው በቢሮው የሴቶች ዘርፍ አመራር እና ባለሙያዎች እንዲሁም የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎችን በራሳቸው እና በቢሮው ስም አመስግነዋል።
አክለውም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ጥቃትችን መከላከል እና መግታት የሚቻለው በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ በመሆኑ በተለያዩ የማስተማር እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎች ላይ ከሀይማኖት አባቶች ጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት እና በቅንጅት እንዲሳተፍ አሳስበዋል።
በቢሮው የስረዐተ ፆታ ጉዳይ ማስረፅ እና ማካተት ዳይሬክተር በሆኑት በወ/ሮ በረከት በቀለ አማካኝነት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን ምንነት እና በህብረተሰቡ ላይ ያለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ሰነድ የቀረበ ሲሆን የቀረበውን ሰነድ አስመልክቶ ተሳታፊዎችም ከስነምግባር ግንባታ ጀምሮ ከእኛ ምን ይጠበቃል በሚል ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱን የቢሮው የበላይ አመራሮች የመሩት ሲሆን በቢሮው የሴቶች ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዝናሽ ከተማ ቢሮው ሴቶችን ከጥገኝነት ለማላቀቅ በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ ከፍትህ አካላት ጋር በህግ ማሻሻያዎች ዙሪያ፣ ከት/ቤት ክበባት ጋር በግንዛቤ መፍጠር ዙሪያ እንዲሁም ከሰላም እና ፀጥታ ጋር የተጀመራቸውን ስራዎች እና የንቅናቄ ስራዎችን በቅንጅት ለመፈፀም የዕለቱ መድረክ አስፈላጊነቱን ጠቁመው ተሳታፊዎችም በዕለቱ ያገኙትን ግንዛቤ ወደየቤታቸው እና ወደ የአካባቢያቸው በመውሰድ ህብረተሰቡን እንዲያስተምሩ ጠቁመዋል።
በዕለቱ የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ከሁሉም ክ/ከተማ የተውጣጡ የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎች፣ የእድር አመራሮች፣ የአረጋዊያን ማህበር አባላት፣የፍትህ አካላት፣የት/ቤት ማህበረሰቦች እና የተለያዩ የሴት አደረጃጀት አባላት የተገኙ ሲሆን በዕለቱ በቀረቡ ፕሮራሞች እና ውይይቶች በቂ ግንዛቤ መቅሰማቸውን በመግለፅ ሀሳቡንም ወደ ቤት እና አካባቢያቸው በመውሰድ የሴቶች እና ሕፃናትን ጥቃት ለማስቀረት እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments